1 Kings 20

ቤን ሀዳድ ሰማርያን ወጋ

1በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ ቤን ሀዳድ መላ ሰራዊቱን በአንድነት አሰባሰበ፤ ከእርሱም ጋር ሠላሳ ሁለት ነገሥታት ከነፈረሶቻቸውና ከነሠረገሎቻቸው አብረውት ነበሩ፤ ወጥቶም ሰማርያን ከብቦ ወጋት። 2ወደ ከተማዪቱም መልእክተኞች በመላክ የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን እንዲህ አለው፤ “ቤን ሀዳድ እንዲህ ይላል፤ 3‘ብርና ወርቅህ የእኔ ነው፤ የሚያማምሩት ሚስቶችህና ልጆችህም የእኔ ናቸው።’ ”

4የእስራኤልም ንጉሥ፣ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ ልክ እንዳልኸው ነው፤ እኔም ሆንሁ የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው” ሲል መለሰለት።

5መልክተኞቹም እንደ ገና መጥተው እንዲህ አሉት፤ “ቤን ሀዳድ የሚለው ይህ ነው፤ ‘ብርህንና ወርቅህን፣ ሚስቶችህንና ልጆችህን እንድትሰጠኝ ልኬብህ ነበር፤ 6ሆኖም ነገ በዚሁ ጊዜ ቤተ መንግሥትህንና የሹማምትህን ቤቶች እንዲበረብሩ፣ ሹማምቴን እልካቸዋለሁ። እነርሱም ማናቸውንም ለአንተ ዋጋ ያለውን ሁሉ በእጃቸው በማስገባት ይወስዱታል።’ ”

7የእስራኤልም ንጉሥ የአገሩን ሽማግሌዎች ሁሉ ጠርቶ፣ “ይህ ሰው እንዴት ጠብ እንደሚፈልግ ታያላችሁ፤ ሚስቶቼንና ልጆቼን፣ ብሬንና ወርቄን እንዳስረክበው በጠየቀኝ ጊዜ አልከለከልሁትም” አላቸው።

8ሽማግሌዎቹና ሕዝቡም ሁሉ፣ “የሚልህን አትቀበለው፤ የጠየቀህንም እሺ አትበለው” አሉት።

9ስለዚህ ለቤን ሀዳድ መልእክተኞች፣ “ለጌታዬ ለንጉሡ፣ ‘እኔ ባሪያህ በመጀመሪያ ያልኸኝን ሁሉ አደርጋለሁ፤ ያሁኑን ጥያቄህን ግን ልፈጽመው አልችልም’ ብላችሁ ንገሩት” አላቸው። መልእክተኞቹም ይህንኑ ይዘው ተመለሱ።

10ከዚያም ቤን ሀዳድ፣ “ለሚከተለኝ ሰው ሁሉ የሰማርያ ዐፈር አንዳንድ ዕፍኝ የሚዳረስ ሳይሆን ቢቀር፣ አማልክት ይህን ያድርጉብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጡብኝ” ሲል ሌሎች መልክተኞችን ወደ አክዓብ ላከ።

11የእስራኤልም ንጉሥ፣ “ ‘ታጥቆ ለጦርነት የሚወጣ ሰው የጦር ትጥቁን እንደ ፈታ ሰው መደንፋት የለበትም’ ብላችሁ ንገሩት” አላቸው።

12ቤን ሀዳድ ይህን መልእክት የሰማው አብረውት የነበሩት ነገሥታት በድንኳኖቻቸው
ወይም ሱኮት በ16 ላይም እንደዚሁ፤
ውስጥ ሆነው በሚጠጡበት ጊዜ ነበር፤ ቤን ሀዳድ ሰዎቹን፣ “በሉ ለጦርነት ተዘጋጁ” አላቸው፤ ስለዚህ ከተማዪቱን ለመውጋት ተዘጋጁ።

አክዓብ ቤን ሀዳድን ድል አደረገ

13በዚያን ጊዜ አንድ ነቢይ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ አክዓብ መጥቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ይህን ብዙ ሰራዊት ታያለህን? ዛሬ በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃለህ’ ” አለው።

14አክዓብም፣ “ይህን የሚያደርገው ማን ነው?” ሲል ጠየቀ።

ነቢዩም፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ይህን የሚያደርጉት የየአውራጃው አዛዥ የሆኑ ወጣት መኰንኖች ናቸው’ ” አለው።

“ታዲያ ጦርነቱን የሚጀምረው ማን ነው?” ሲል ጠየቀ።

ነቢዩም፣ “አንተው ትጀምራለህ” ብሎ መለሰ።

15ስለዚህ አክዓብ የየአውራጃው አዛዥ የሆኑትን ሁለት መቶ ሠላሳ ሁለት ወጣት መኰንኖች ጠራ፤ ከዚያም የቀሩትን እስራኤላውያን ሰበሰበ፤ እነዚህም በአጠቃላይ ሰባት ሺሕ ነበሩ። 16እነርሱም ቤን ሀዳድና ከእርሱ ጋር ተባብረው የነበሩት ሠላሳ ሁለቱ ነገሥታት በድንኳኖቻቸው ውስጥ ሰክረው ሳለ እኩለ ቀን ላይ መጡ። 17በግንባር ቀደምትነት የወጡት ግን፣ የየአውራጃው አዛዥ የሆኑት ወጣት መኰንኖች ነበሩ።

በዚህ ጊዜ ቤን ሀዳድ ሰላዮች ልኮ ነበርና እነርሱም፣ “ሰዎች ከሰማርያ ወጥተው ወደዚህ በመምጣት ላይ ናቸው” ብለው ነገሩት።

18እርሱም፣ “አመጣጣቸው ለሰላምም ይሁን ለጦርነት ከነሕይወታቸው ይዛችሁ አምጧቸው” አለ።

19የየአውራጃው አዛዥ የሆኑ ወጣት መኰንኖችም ሰራዊቱን አስከትለው ከከተማዪቱ ወጡ፤ 20እያንዳንዱም በፊቱ የገጠመውን ጠላት ገደለ፤ ሶርያውያን ሸሹ፤ እስራኤላውያንም ያሳድዷቸው ጀመር። የሶርያ ንጉሥ ቤን ሀዳድ ግን በፈረሱ ላይ ሆኖ ከጥቂት ፈረሰኞቹ ጋር አመለጠ። 21የእስራኤል ንጉሥ አክዓብም ወደ ፊት በመግፋት ፈረሶችንና ሠረገሎችን ማረከ፤ በሶርያውያንም ላይ ከባድ ጕዳት አደረሰባቸው።

22ከዚያም በኋላ ነቢዩ ወደ እስራኤል ንጉሥ መጥቶ፣ “በሚመጣው የጸደይ ወራት የሶርያ ንጉሥ ተመልሶ ይመጣብሃልና በርታ፤ ምን ማድረግ እንዳለብህም ዕወቅ” አለው።

23በዚያኑ ጊዜም የሶርያ ንጉሥ ሹማምት እንዲህ ሲሉ መከሩት፤ “አማልክታቸው የኰረብታ አማልክት ናቸው፤ ያየሉብንም ከዚህ የተነሣ ነው። በሜዳ ላይ ብንገጥማቸው ግን እኛ እንደምናይልባቸው አያጠራጥርም። 24እንግዲህ እንዲህ አድርግ፤ ነገሥታቱን በሙሉ ከአዛዥነታቸው አስነሣ፤ በቦታቸውም ሌሎች ሹማምት አድርግ። 25ከእስራኤል ጋር በሜዳው ላይ እንዲጋጠም በፈረሱ ፈንታ ፈረስ፣ በሠረገላው ፈንታ ሠረገላ በመተካት፣ እንደ ተደመሰሰው ያለ ሰራዊት አቋቁም፤ ከዚያ በኋላ ከእነርሱ ይበልጥ እኛ እንደምንበረታ አያጠራጥርም።” ንጉሡም ባቀረቡት ሐሳብ ተስማማ፤ እንዳሉትም አደረገ።

26በተከታዩም የጸደይ ወራት ቤን ሀዳድ ሶርያውያንን አሰባስቦ እስራኤልን ለመውጋት ወደ አፌቅ ወጣ። 27እስራኤላውያንም እንደዚሁ ተሰብስበው ስንቅ ከተሰጣቸው በኋላ ሊገጥሟቸው ተሰልፈው ወጡ። ሶርያውያን አገር ምድሩን ሞልተውት ሳለ፣ እስራኤላውያን ግን እንደ ሁለት ትንንሽ የፍየል መንጋ ሆነው ከፊት ለፊታቸው ሰፈሩ።

28የእግዚአብሔርም ሰው ወጥቶ ለእስራኤል ንጉሥ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሶርያውያን እግዚአብሔር የኰረብታ እንጂ የሸለቆ አምላክ አይደለም ብለዋልና ይህን ስፍር ቍጥር የሌለው ሰራዊት በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ አንተም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃለህ’ ” አለው።

29በየሰፈሩበትም ቦታ ሰባት ቀን ከተፋጠጡ በኋላ በሰባተኛው ቀን ጦርነት ገጠሙ። እስራኤላውያንም በአንዲት ጀምበር ከሶርያውያን ሰራዊት መቶ ሺሕ እግረኛ ገደሉ። 30የቀሩት ወደ አፌቅ ከተማ ሸሹ፤ በዚያም በሃያ ሰባቱ ሺሕ ላይ ቅጥሩ ተንዶ ወደቀባቸው። ቤን ሃዳድም ወደ ከተማዪቱ ሸሽቶ በመሄድ ወደ አንዲት እልፍኝ ገብቶ ተደበቀ።

31ሹማምቱም፣ “የእስራኤል ቤት ነገሥታት መሓሪዎች መሆናቸውን ሰምተናል፤ አሁንም እንነሣና በወገባችን ላይ ማቅ ታጥቀን፣ በራሳችን ላይ ገመድ ጠምጥመን ወደ እስራኤል ንጉሥ እንሂድ፤ ምናልባትም ሕይወትህን ያተርፋት ይሆናል” አሉት።

32እነርሱም በወገባቸው ላይ ማቅ ታጥቀው፣ በራሳቸው ላይ ገመድ ጠምጥመው ወደ እስራኤል ንጉሥ በመሄድ፣ “አገልጋይህ ቤን ሀዳድ፣ ‘እባክህ በሕይወት እንድኖር ፍቀድልኝ’ ብሎ ይለምንሃል” አሉት።

ንጉሡም፣ “እስካሁን በሕይወት አለን? ወንድሜ እኮ ነው” አለ።

33ሰዎቹም ይህን በደግ በመተርጐም ቃሉን ከአፉ ቀበል አድርገው፤ “አዎን ቤን ሀዳድ ወንድምህ ነው” አሉት።

ንጉሡም፣ “በሉ ሂዱና አምጡት” አላቸው፤ ቤን ሃዳድም በመጣ ጊዜ፣ አክዓብ ሠረገላው ላይ እንዲወጣ አደረገው።

34ቤን ሃዳድም፣ “አባቴ ከአባትህ የወሰዳቸውን ከተሞች እመልሳለሁ፤ አባቴ በሰማርያ እንዳደረገው ሁሉ፣ አንተም በደማስቆ የራስህን ገበያ ማቋቋም ትችላለህ” አለው።

አክዓብም፣ “እንግዲያውስ ስምምነት አድርገን በነጻ እለቅቅሃለሁ” አለው፤ ስለዚህም ከእርሱ ጋር የውል ስምምነት አድርጎ ለቀቀው።

አንድ ነቢይ በአክዓብ ላይ ፈረደ

35ከነቢያት ልጆች አንዱ ጓደኛውን በእግዚአብሔር ቃል ታዞ፣ “ምታኝ” አለው፤ ሰውየው ግን ፈቃደኛ አልሆነም።

36ስለዚህም ነቢዩ፣ “ለእግዚአብሔር ባለ መታዘዝህ፣ ከእኔ ተለይተህ እንደ ሄድህ አንበሳ ይገድልሃል” አለው። ሰውየው ከሄደ በኋላ አንበሳ አግኝቶ ገደለው።

37ነቢዩም ሌላ ሰው አግኝቶ፣ “እባክህ ምታኝ” አለው። ስለዚህ ያ ሰው መትቶ አቈሰለው። 38ከዚያም ነቢዩ ሄዶ ከመንገድ ዳር በመቆም፣ ንጉሡን ይጠባበቅ ጀመር። የራሱን መጠምጠሚያ ወደ ታች አውርዶ ዐይኖቹን በመሸፈንም፣ ማንነቱ እንዳይታወቅ አደረገ። 39ንጉሡ በዚያ በሚያልፍበትም ጊዜ፣ ነቢዩ ጠርቶት እንዲህ አለው፤ “እኔ አገልጋይህ በተፋፋመው ጦርነት መካከል ገብቼ ሳለሁ፣ አንድ ሰው ምርኮኛ ይዞ መጥቶ ‘ይህን ሰው ጠብቅ፤ ቢያመልጥ በገመዱ ትገባለህ ወይም አንድ መክሊት
34 ኪሎ ግራም ያህል ነው።
ብር ትከፍላለህ’ አለኝ።
40‘ታዲያ እኔ አገልጋይህ ሥራ በዝቶብኝ ወዲያ ወዲህ ስል ሰውየው አምልጦ ሄደ።’ ”

የእስራኤልም ንጉሥ፣ “ራስህ ፈርደሃል፤ ይኸው ይፈጸምብሃል” አለው።

41ከዚያም ነቢዩ መጠምጠሚያውን በፍጥነት ከዐይኑ ላይ አነሣ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ያ ሰው ከነቢያት አንዱ መሆኑን ዐወቀ። 42ነቢዩም ንጉሡን አለው፤ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እኔ ፈጽሞ ይገደል
የዕብራይስጡ ቃል ሰውን ወይም ቍስን ፈጽሞ በማጥፋት ለእግዚአብሔር መስጠት የሚለውን ያመለክታል።
ያልሁትን ሰው ለቅቀኸዋልና በገመዱ ትገባለህ፤ በሕዝቡም ፈንታ ያንተ ሕዝብ በገመዱ ይገባል።’ ”
43የእስራኤልም ንጉሥ ተበሳጭቶና ተቈጥቶ ሰማርያ ወዳለው ቤተ መንግሥቱ ሄደ።

Copyright information for AmhNASV